መቃወምም ሆነ መደገፍ መብት ነው። በውሸት ዜና ለማትረፍ መሞከር ግን አስነዋሪ ነው።
ባለፉት 6 ወራት ብዙ የሚባሉ ሸጋ ክንዋኔዎች የተከናወኑ ቢሆንም በተጓዳኝም ጥቂት የማይባሉ ፈታኝ አጋጣሚዎችንም አስተውለናል። ሆን ተብሎ የውሸት መረጃ በመልቀቅ በህዝቦች መካከል ጥርጣሬ በመፍጠር ለፖለቲካ ትርፍ መሯሯጥ በተደጋጋሚ ይስተዋላል። ያልሆነው እንደሆነ አድርጎ በማውራት፤ ያልተከሰተውን እንደተከሰተ አድርጎ የውሸት መረጃ በመልቀቅ አለመራጋጋት ለመፍጠር ሲሞከር እናያለን። ብዙ መስራት ሲቻል በመጠላለፍ
ጊዜ ማባከኑ ምን ይጠቅማል? ዛሬ በጎ ነገር በመስራት ነገ የተሻለ ቀን እንዲሆን ማድረግ የሚያስችል አቅም አለን። ኢትዮጵያ የብዙሃን
ሀገር ነች። በፈሪሃ እግዚአብሄር የምተታወቅ ሀገር። አንተ ትብስ፤ አንቺ ትብሽ የመባባል የቆየ የአብሮነትና የመቻቻል እሴቶች የዳበሩባት
ሀገር ናት። አኩሪ የሆነ ታሪክ አላት ሀገር። ይህ ሁሉ ሊያኮራንና ወደፊት የበለጠ ለመስራት እንድንተጋ ሊያደርጉን ይገባል
እንጂ ወደ ኋላ ሊጎትቱን አይገባም።
የጋራ ጠላታችን ድህነት ነው። ይህም ከመልካም አስተዳደር እጦት የመጣ ነው። በስልጣን
ላይ ያለው የዶ/ር አቢይ አህመድ መንግስት በሀገራችን ለመጀመሪያ ጊዜ በሚባል ደረጃ የኢትዮጵያውያንን የልብ ትርታ ማዳመጥ የሚችል
ስርዓት እንዲመጣ ደፋ ቀና እያለ ባለበት በዚህ ጊዜ ብንችል በመደገፍ የበኩላችንን ማድረግ አለበለዚያ እንቅፋት በመሆን ጥቁር አሻራ
ጥለን ላለማልፍ ጥረት እናድርግ። ነገ በተስፋ የተሞላ ቀን እንዲሆን ዛሬ ተግተን እንስራ። ልጆቻችን፣ የልጅ ልጆቻችን ባጠቃላይ መጪው ትውልድ የወደፊት ህይወቱ አስደሳችና የተቃና እንዲሆን ዛሬን ሳናሰልስ በበጎ ነገር እናሳልፈው።
ዛሬን በጎ ነገር ሰርተን ነገን እንገንባ።