29 August 2018

ዲያስፖራው ለሀገሩ


በውጭ የምንኖር ኢትዮጵያውያን በአብዛኛው ጊዜ ስለ ሀገር ጉዳይ ከመወያየት ተቆጥበን አናውቅም:: አልፎ አልፎም መከራከራችን አይቀርም:: በሃሳብ ልንለያይም እንችላለን:: በሃሳብ መለያየት ክፋት የለውም። በሃሳብ መለያየታችን ለዲሞክራሲ ግንባታ የበኩላችንን ከማድረግ ሊያግደን አይገባም:: አብረን ከመስራትም ሊያግደን አይገባም::

ዛሬ ነገ ሳንል  ተግባራዊ እንቅስቃሴ በማድረግ በሀገራችን ኢትዮጵያ የተጀመረውን የለውጥ ጉዞ  ማገዝ ኢትዮጵያዊ ኃላፊነታችንና ግዴታችን ነው:: ተግባር ከብዙ ቃል በላይ ይናገራል ይባላልና እራሳችንን በተግባር የምንፈትሽበት ጊዜ ነው:: ሀገራችን ከአምባገነናዊ ሥርዓት ተላቃ በሽግግር ላይ  ያለች እንደመሆኗ መጠን ከምንም ጊዜ በላይ የልጆቿ እገዛ  ያስፈልጋታል።

ዲያስፖራው  ለውጡን በብዙ መልኩ ማገዝ ይቸላል፣ ዋናው ቁርጠኝነት ነው። 

በሀገራችን የተከሰተው ለውጥ ስር ነቀልና ዘላቂ እንዲሆን ከምንም በላይ የተቋማት ግንባታ ያስፈልጋል:: ሲቪክ ማህበራት፤ ነፃ የሚዲያ ተቋማት፤ ከፖለቲካ ፓርቲ ተፅእኖ የተላቀቀ ሲቪል ሰርቪስ እና ሌሎችም ለዲሞክራሲያዊ ሥርዓት አስፈላጊ የሆኑ ግብዓቶች በሙሉ እንዲሟሉ ዲያስፖራው በብዙ መልኩ እገዛ ማድረግ ይችላል። ይህ ተግባራዊ እንዲሆን ሁሉም በሆደ ሰፊነትና ይቅር ባይነት መንፈስ ሊነሳሳና ነገ የተሻለ ቀን እንዲሆን ሊሰራ ይገባል። ትናንት አብረን ስላልሰራን ነገም አብረን መስራት አንችልም የሚል አመለካከት ጊዜው ያለፈበትና ያረጀ ነው። በፖለቲካው ዓለም ዘላለማዊ ወዳጅ ወይም ዘላለማዊ ጠላት የለም ይባላል። ሁሉም በህሊናው ልክ ነው የሚለውን ነገር ለማሳካት ነው የሚሰራው። በዚህ ሂደት ውስጥ ደግሞ ለድርድር የማይቀርቡ ነገሮች እንደሚኖሩት ሁሉ የጋራ የሚያደርጉን ብዙ ነገሮች አሉ። ኢትዮጵያ የሁላችን ነች። ኢትዮጵያ የጋራችን ነች። ከአንድ ቤተሰብ የተፈጠሩ ግለሰቦች በእናታቸው አይደራደሩም። ወፈርችም ቀጠነች፤ አጠርችም ረዘመች፤ ደሃም ሆነች ሀብታም፤ እናት ሁሌም እናት ነች። ኢትዮጵያም ኢትዮጵያ ናት።

ኢትዮጵያውያን ዲያስፖራዎችን አንድ የሚያደርገን ከምንም በላይ ኢትዮጵያዊነት ነው። ሀገራችን በበጎ እንጂ በክፉ ስሟ አንዲነሳ አንፈልግም። ወደድንም ጠላን ሀገራችን ሀገራችን ነች።  የሀገራችን በኢኮኖሚ ወደ ኋላ መቅረት ጠንክረን በህብረት ያለመስራታችን ውጤት ነው። ለዚህም የነበሩት ስርዓቶች ተፅዕኖ ያደረጉብን መሆኑ የማይካድ ሲሆን በአሁኑ ሰዓት ያገኘነውን መልካም አጋጣሚ በመጠቀም ሀገራችንን ልናግዛትና የበኩላችንን ልናደርግላት ይገባል፣ ይቻላልም። ላለፉት አያሌ አመታት በዓለም ዙሪያ የተበተኑት ኢትዮጵያውያን በየሀገሮቹ ካሉት ኤምባሲዎች ጋር ያላቸው ግንኙነት እጅግ በጣም አናሳ ነበር። በዚህም ምክንያት በዲያስፖራውና በኤምባሲዎች መካከል ያለው ግንኙነት ጥርጣሬ የበዛበትና ብዙ ወደፊት መሄድ የማይችል ነበረ። ይህ የቆየና ስር የሰደደ አመለካከት ከጊዜው ጋር ሊለወጥ ይገባል። መጥፎ ነገሮችን እንደምናወግዝ ሁሉ በጎ ነገሮችን ደግሞ ማወደስና ማበረታታት ይገባል። ኢትዮጵያዊ አብሮ መብላት እንጂ አብሮ መስራት አይችልም የሚለውን የቆየ አባባል ማክሸፍ ይገባል። በልዩነት ላይ ተስማምቶ አብሮ መስራት እንደሚቻል በተግባር በማሳየት የተለወጥን ሰዎች መሆናችንን ማሳየት አለብን። ጊዜው ሲደርስ ዜጎች ከኤምባሲዎቻቸው ጋር መልካም ግንኙነት ፈጥረው ብዙ ለሃገር የሚበጅ ስራ መስራት ይቻላሉ። ያኔ ሁሉም ይሆናል። እስከዚያው ግን ዲያስፖራው በግሉና በተደራጀ መልኩ ብዙ ነገሮችን ማከናወን ይችላል።  

የሚከተሉትን ማከናወን ለሞራል እርካታ ከማገዙም በላይ ሀገራዊ ግዴታን ለመወጣት ይጠቅማል።

1.       የውይይት መድረኮችን፣ ኮንፈራንሶችን፣ ልዩ ልዩ ዐውደ ጥናቶችን በማዘጋጀት ህዝባችን የተገኙትን ለውጦች እውቀቱን፣ ገንዘቡን፣ ጊዜውን በመስጠት በተግባር ማገዝ እንዲችል ማበረታታት።
2.    ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመነጋገር ዜጎች የገንዝብ እገዛ እንዲያደርጉና ገንዘባቸውም ለታቀደለት ዓላማ እንዲውል ንቁ ተሳትፎ ማድረግ።
3.       ዜጎቻችን ወደ ሀገራቸው በመሄድ እወቀታቸውንና ጊዜያቸውን ለወገኖቻቸው እንዲያካፍሉ ማበረታታት።
4.       ዜጎቻችን ከሀገር ቤት የሚያገኙትን እውቀትና ልምድ በሚኖሩበት ሀገር ለሚገኙ ወገኖች ማካፈል የሚችሉበትን መድረክ ማመቻቸት።
5.       ዜጎች የውጭ ትምህርት እድል እንዲያገኙ ጥረት ማድረግ፣ አስፈላጊ ሆኖ ሲግኝ በተደራጀ መልኩ ማገዝ።
6.       ኢንቨስትመንት ወደ ሀገር ቤት እንዲገባ ማበረታታት::
7.       ሀገራችን ከቱሪስቶች ጉብኝት የውጭ ምንዛሬ ልታገኝ የምትችለበትን ሁኔታ መፍጠር
እነዚህንና ሌሎች ተግባራትን በተደራጅ መልኩ በማከናወን ሀገራዊ ግዴታን በመወጣት ከህሊና ወቀሳም መዳን ይቻላል። ከምንም በላይ ግን ለዲሞክራሲያዊ ተቋማት ግንባታ ዲያስፖራው ከፍተኛ እገዛ ማድረግ ይችላል ። ይጠበቅበታልም።

ቸር እንሰንብት።


21 August 2018

ለበሬ ወለደ ዜና ቦታ የለንም


                             

የሶሻል ሚዲያ የውሸት ዜናዎች (Fake News) ሊያሸብሩን አይገባም!

በሀገራችን የተከሰተውን ለውጥ ተከትሎ ብዙ በሬ ወለደ ዜናዎች በሶሻል ሚዲያ ውጤቶች በተለይም በፌስ ቡክና ቲዩብ ( Facebook and You tube) በብዛት ተሰራጭተው እናያለን። እነዚህ የበሬ ወለደ ዜናዎች ብዙሃን ወገኖቻችንን ሊያሳስቱና ሊያስጨንቁ ይችላሉ። ህዝባችን የውሸት ዜናዎችን አጥብቆ መታገል ይገባዋል። ከምንም በፊት ለነዚህ የውሸት ዜናዎች ቦታ ባለመስጠት፤ አስፈላጊ ከሆነም የውሸት ዜናዎቹ በሚለቀቁበት ጊዜ የወሬዎቹን ምንጭ በመጠየቅ ብዙ ጥፋት ሳያስከትሉ ሊያስቆማቸው ይገባል።

የወሸት ዜናዎች በተለያዩ ምክንያቶች ሊፈጠሩ የሚችሉ ሲሆን የተለያየ አላማዎችም አሏቸው።

1. የፖለቲካ ለውጡን ለማወክ የሚደረግ ጥረት፥ በሀገራችን የተከሰተው ለውጥ ደጋፊ እንዳለው ሁሉ ተቃዋሚም አለው። ይህ ደግሞ በለውጥ ሂደት ውስጥ ብዙ ጊዜ የሚከሰት ነው። የፖለቲካና የኢኮኖሚ ጥቅማቸው የሚነካባቸው ግለሰቦችና ድርጅቶች በተቻላቸው መጠን የለውጥ ሂደቱን ከማወክ አይቆጠቡም። ለዚህም የተቻላቸውን ያህል በማድረግ ለወጡ እንዳይሳካና ህዝቡ በለውጡ ላይ ጥርጣሬ እንዲኖረው ለማድረግ ብዙ ጥረት ያደርጋሉ። ለውጡ እንዲቀለበስ ሌት ተቀን ተግተው ከመስራት አይቆጠቡም። እኩይ አላማቸውን ለማሳካት ብዙ ገንዘብ በማውጣት የተቻላቸውን ሁሉ ያደርጋሉ። ይህ የውንብድና ሥራ ብዙም ስለማያስኬድ በዚህ ተልካሻ ተግባር ላይ የሚሳተፉ ግለሰቦችና ድርጅቶች ሌሎች ለውጥ የማደናቀፍ ተግባራት ላይ ከመሳተፍ አይቆጠቡም። ህዝባችን በሀገራችን ለተከሰተው ለውጥ ዘብ በመሆን ለውጡን እንደ ዓይኑ ብሌን ሊጠብቀው ይገባል።

2. የገንዘብ ፍቅር፤ በገንዘብ ፍቅር የተለከፈ ሰው ለገንዘብ ሲል ብዙ አሳፋሪ ተግባራት ሊፈጽም ይችላል። በተለይ ከዩ ቲዩብ (You Tube) ለምትገኝ ጥቃቅን ጥቅማጥቅም ኃላፊነት የጎደላቸውና ምንጭ አልባ የውሸት ዜናዎች ሲለጥፉ እያየን ነው። በእንደዚህ አይነቱ ተልካሻ ተግባራት ላይ የሚሳተፉ ሰዎች ብዙውን ጊዜ የሚያሳስባቸው ምን ያህል ሰው የለጠፉትን ቪዲዮ እንዳየው ማወቅ በቻ ነው። ይህ ተግባር አሳፋሪ ነው። ሊታረምም ይገባል። ህዝባችንም አጥብቆ ሊታገለው ይገባል።

3. 15 ደቂቃ ታዋቂነት መሻት (15 minutes social media fame) የተለያዩ የውሸት ዜናዎችን በተለይ በፌስ ቡክ ላይ በመለጠፍ ለሚያገኙት ላይክ ( like ) ብቻ የሚጨነቁና ያም ታዋቂነት የሚያፈራላቸው የሚመስላቸወ ሰዎች አሉ። ይህ አይነቱ ተግባር በአብዛኛው በፌስ ቡክና ትዊተር ሲከሰት ይስተዋላል። ህዝባችን የዜናዎችን ምንጭ የመጠየቅ ባህል ሊያዳበር ይገባል። ሁሌም ሳናታክት ዜናው እንዴትና ከማን እንደመጣ መጠየቅ አለብን።

4. በየዋህነት የተነገረውን ሁሉ ማሰራጨት፤ ከዘመዴ፣ ከጓደኛዬ፣ ከውስጥ አዋቂ ምንጭ ያገኘሁት ነው በሚል የፈጠራና የውሸት ዜናዎች ሲሰራጩ ይታያል። አልፎ አልፎ የምናያቸው የውሸት ዜናዎች በየዋህነት የሚሰራጩ ናቸው። ጥንቃቄ ማድረግ ይገባል። በተለይ ከውስጥ አዋቂ ምንጭ እንዳገኘሁት የምትለዋ ሊሰመርባት ይገባል። ግልፅ መሆን ያለበት ሁላችንም የውስጥ አዋቂ ምንጭ ሊኖረን አይችልም። 100 ሚሊዮን ህዝበ ባለባት ሀገር ላይ 100 ሚሊዮን የውስጥ አዋቂ ምንጭ እንደመጥቀስ ነው። ጎበዝ ጦር ከፈታው ወሬ የፈታው ይሉ የለ አበው። ጠንቀቅ ማለት ይገባል። መጠየቅ፤ ተጨማሪ ምርምር ( research )ማድረግ ይገባል።
ለውጡን የመጠበቅ ኢትዮጵያዊ ግዴታ አለብን። በየጊዜው የሚፈጠሩ የውሸት ዜናዎች ሊያውኩንና ሊያሳስቱን አይገባም። አበከረንም ልንታገላቸውም ይገባል።

ለነ በሬ ወለደ ቦታ ባለመስጠት የለውጥ ጉዟችንን በጋራ እንጓዝ። ኢትዮጵያችንን በህብረትና በዓላማ ፅናት እንጠብቃት።

3 August 2018

ኢትዮጵያችንን በተደራጀ መልኩ እናግዛት ፤ ሀገራችንን እኛ ካላገዝናት ማን ያግዛታል?


ኢትዮጵያዊነት ፍቅር ፤ ኢትዮጵያዊነት መቻቻል ፤ ኢትዮጵያዊነት መከባበር ፤ ኢትዮጵያዊነት መንፈስ፤ ኢትዮጵያዊነት ፀጋ ፤ ኢትዮጵያዊነት የታላቅነት ምሳሌ ፤ ኢትዮጵያዊነት ብዙሃንነት ፤ ኢትዮጵያዊነት ህብረት ፤ ኢትዮጵያዊነት የአኩሪ ታሪክ ባለቤትነትን ያካተተ ውስጡ ትልቅ ሚስጥር ያለው ነው፥፥ እነዚህንና ሌሎችን ኢትዮጵያዊ እሴቶች መሠረት በማድረግ በሀገራችን ኢትዮጵያ የተጀመረውን የለውጥ ጉዞ ተግባራዊ በሆነ መልኩ ማገዝ ከያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ የሚጠበቅ ነው፥፥

በአለም ዙሪያ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያኖች ለሀገራችው ያላቸው ፍቅር በጣም የሚያኮራ ነው። ብዙዎቹ ሀገር ቤት በነበረው የፖለቲካ ሁኔታ የተነሳ ለአያሌ ዓመታት በየሀገሮቹ በሚገኙ ኤምባሲዎች በራፍ ላይ በመገኘት ቅሬታቸውን ሲያሰሙ የቆዩ ሲሆን አብዛኞቹም ኤምባሲዎቹ የነሱ አይመስሏቸውም ነበር።  የዶ/ር አቢይ አህመድን ወደ ስልጣን መምጣት ተከትሎ ይህ አመለካከት የተቀየረ ይመስላል። ህዝባችን የተገኙትን ለውጦች እውቀቱን፣ ገንዘቡን፣ ጊዜውን በመስጠት በተግባር ማገዝ ይጠበቅበታል፥፥ ጊዜው የመደመር፣ የይቀርታ ፤ የመቻቻልና በሀገራችን የተጀመረውን የለውጥ ጉዞ በጋራ በመሆን የምንንከባከብበትና ለዘላቂ የዲሞከራሲያዊ ሦርዓት ግንባታ በጋራ የምንሰራበት እንደመሆኑ መጠን ሁሉም ዜጋ የበኩሉን የማድረግ ግዴታ አለበት። በብዙ ሀገራት ተግባራዊ እንቅስቃሴዎችም እንደተጀመሩ ማየት ይቻላል። ይህ ተግባራዊ እንቀስቃሴ ዘላቂና ውጤታማ እንዲሆን ከመቼውም ጊዜ በበለጠ በመደራጀትና በታቀደ መልኩ መስራት ጠቀሜታው የበዛ ነው። መነጋገር ፣ መደራጀትና በእቅድ መስራት ከተቻለ ብዙ ማከናወን የሚያስችል አቅም ሊኖረን ይችላል፥፥ በጋራ በመሆንና በእቅድ መስራት ከቻልን ትኩረታችን አስፈላጊ በሆኑ ነገሮች ላይ ይሆናል፥፥ ሁላችንም ተመሳሳይ ስራ ላይ ከማተኮር በተለያየ ተባራት ላይ በመሳተፍ ሀገራችንን ሁለገብ በሆነ መልኩ ማገዝ እንቸላለን፥፥ ለሁላችንም የሚሆን የሀገር ግንባታ ሥራ አለ፥፥ ሁላችንም የሀገራችን አምባሳደሮች መሆናችንንም መዘንጋት የለብንም፥፥ አጋጣሚዎችን በመጠቀም ወደ ሀገራችን ኢንቬትመንት እንዲገባ የበኩላችንን ድርሻ የመወጣት ኢትዮጵያዊ ኃላፊነትም አለብን፥፥ 

ወደ ተግባራዊ እንቀስቃሴ ከመግባታችን በፊት የተወሰኑ ጥያቄዎችን ማየት ተገቢ ይሆናል ፥፥

1.     ሀገራችን ምን ያስፈልጋታል? ሀገራችን ምን አላት?
2.     ሌሎች ወገኖች ምን እያደረጉ ነው?
3.     ለሀገራችን ከሚያስፈልገው ውስጥ የትኛውን በተሻለና በተደራጀ መልኩ ማገዝ እንችላለን?
4.     ይህንን ማከናወን የሚያስችል ስብስብ ውይም ግሩፕ አለን ወይ?
5.     እቅዳችንን ማገዝ የሚችሉ ተቋማትና ታዋቂ ግለሰቦች አሉ?
6.     ከነዚህ ተቋማትና ታዋቂ ግለሰቦች ጋር ትውውቀና ግንኙነት አለን?
7.     እቅዳችንን እንዴት ነው ተግባራዊ የምናደርገው?
8.       እቅዳችንን ለህዘባችንና ለሚመለከታቸው ሁሉ እንዴት ነው የምናሳውቀው?
9.     የጊዜ ሰሌዳችን ምን ይመስላል?

ከላይ የተጠቀሱትንና መሰል ጥያቄዎችን በመመለስ የተደራጀ፣ ዘለቄታ ያለወና ብዙሃንን ማሳተፍ የሚችል ተግባራዊ ስራዎቸን መስራት እንችላለን፥፥ ስለ ሀገር መነጋገርና በጋራ መስራት ለሁላችንም ይበጃል፥፥ በሀገራችን ጉዳይ ሁላችንም የሚያገባንን ያህል ሀገራቸንን በተደራጀ መልኩ ማገዝ ብንችል ወጤቱ ሁላችንንም የሚያኮራና ከዘመን ዘመን የሚሸጋገር ሊሆን ይቸላል፥፥ ለመጪው ትውልድም የተሻለ ነገር አስተምረን ማለፍ እንቸላለን፥፥ በተደራጀና ሁሉን ባሳተፈ መልኩ መስራት ከቻልን ሀገራችንን በሁሉ መልኩ ልናግዛት እንችላለን፥፥ ይህንን ተግባራዊ የማድረጊያው ጊዜ ደግሞ አሁንና አሁን ብቻ ነው፥፥

ቸር እንሰንብት፥፥

Memorable days in Nepal, a country in between mountains

A few months ago I had an email from Katherine Hughes-Fraitekh, Co-Founder and Director of  Solidarity 2020 and Beyond  about an event that ...