የዲያስፖራ ኮሚኒቲዉ ወደ ሀገር ቤት በብዛት ለመግባት እየተዘጋጀ ባለበት በአሁኑ ወቅት ብዙ ነገሮችን ማሰብ ተገቢ ነው። ዲያስፖራው ወደ ሀገር ቤት መግባቱ በራሱ ፖለቲካዊ ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጠቀሜታው ብዙ ነው። ዲያስፖራው ብዙ ማድረግ ይቻላል። ይህ ጊዜ ከምንም ጊዜ በላይ ለሀገራችን ገንዘባችንን ፣ እውቀታችንን ፣ ጉልበታችንን ፣ ልምዳችንን የምንሰጥበትና በጦርነት ለተጎዱ ወገኖች ተግባራዊ ስራ በመስራት ለወገኖቻችን አለኝታ መሆናችንን የምናሳይበት ነው:: በሀገር ቤት ያሉ እንደ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ ዲያስፖራ ኤጀንሲ ፣ የቱሪዝም ሚኒስቴር ፣ አደጋና መከላከል ኮሚሽን፣ ትምህርት ሚኒስቴር ፣ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴርና ሌሎች ሲቪክና ልዩ ልዩ ተቋማት በተቀናጀና በተናበበ መልኩ አጋጣሚውን ሊጠቀሙበት ይገባል። ዲያስፖራው በቡድን በመሆነ በተለይ በጦርነቱ በተጎዱ አካባቢዎች እንደ ትምህርት ቤት ግንባታ ፣ የጤና ተቋማት ግንባታና በጣም ወሳኝ በሆኑ የመሰረተ ልማት ስራ ላይ እንዲሰማራ ሁኔታዎች ሊመቻቹለት ይገባል። ዲያስፖራው ለሀገሩ ያለውን ፍቅር በዓለም ዙሪያ አሳይቷል። በተጨማሪው ብዙ አቅም እንዳለውም አሳይቷል። ዋናውና ወሳኙ ጥያቄ ይህንን የዲያስፖራውን እምቅ አቅም ለመጠቅም ዝግጁ ነን ወይ የሚለው ላይ ነው። ለዚህ ተግባራዊነት በተለይ የውጭ ጉዳይ ሚ/ር ከፍተኛ ኃላፊነት አለበት።
ከላይ የተጠቀሱት አስቸኳይና ወቅታዊ ተግባራትን ማከናወን እንዳለ ሆኖ ዘላቂና አሳታፊ እቅዶችን ማዘጋጀትና ለተግባራዊ እንቅስቃሴ መዘጋጀት ኢትዮጵያ በጋራ ወደ ከፍታ ለመውሰድ ጠቀሜታው ብዙ ነው።
በተጨማሪም ዲያስፖራው በግሉና በተደራጀ መልኩ ብዙ ነገሮችን ማከናወን ይችላል።
የሚከተሉትን ማከናወን ለሞራል እርካታ ከማገዙም በላይ ሀገራዊ ግዴታን ለመወጣት ይጠቅማል።
1. የውይይት መድረኮችን፣ ኮንፈራንሶችን፣ ልዩ ልዩ ዐውደ ጥናቶችን በማዘጋጀት ህዝባችን የተገኙትን ለውጦች እውቀቱን፣ ገንዘቡን፣ ጊዜውን በመስጠት በተግባር ማገዝ እንዲችል ማበረታታት።
2. ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመነጋገር ዜጎች የገንዝብ እገዛ እንዲያደርጉና ገንዘባቸውም ለታቀደለት ዓላማ እንዲውል ንቁ ተሳትፎ ማድረግ።
3. ዜጎቻችን ወደ ሀገራቸው በመሄድ እወቀታቸውንና ጊዜያቸውን ለወገኖቻቸው እንዲያካፍሉ ማበረታታት።
4. ዜጎቻችን ከሀገር ቤት የሚያገኙትን እውቀትና ልምድ በሚኖሩበት ሀገር ለሚገኙ ወገኖች ማካፈል የሚችሉበትን መድረክ ማመቻቸት።
5. ዜጎች የውጭ ትምህርት እድል እንዲያገኙ ጥረት ማድረግ፣ አስፈላጊ ሆኖ ሲግኝ በተደራጀ መልኩ ማገዝ።
6. ኢንቨስትመንት ወደ ሀገር ቤት እንዲገባ ማበረታታት።
7. ሀገራችን ከቱሪስቶች ጉብኝት የውጭ ምንዛሬ ልታገኝ የምትችለበትን ሁኔታ መፍጠር ።
8. ዜጎች ህጋዊ በሆኑ የገንዘብ አስተላላፊ ድርጅቶች በመጠቀም ሀገራችን የወጭ ምንዛሪ እንድታገኝ ማድረግ።
እነዚህንና ሌሎች ተግባራትን በተደራጅ መልኩ በማከናወን ሀገራዊ ግዴታን በመወጣት ከህሊና ወቀሳም መዳን ይቻላል። ከምንም በላይ ግን ለዲሞክራሲያዊ ተቋማት ግንባታ ዲያስፖራው ከፍተኛ እገዛ ማድረግ ይችላል ። ይጠበቅበታልም።