Wednesday, 29 August 2018

ዲያስፖራው ለሀገሩ


በውጭ የምንኖር ኢትዮጵያውያን በአብዛኛው ጊዜ ስለ ሀገር ጉዳይ ከመወያየት ተቆጥበን አናውቅም:: አልፎ አልፎም መከራከራችን አይቀርም:: በሃሳብ ልንለያይም እንችላለን:: በሃሳብ መለያየት ክፋት የለውም። በሃሳብ መለያየታችን ለዲሞክራሲ ግንባታ የበኩላችንን ከማድረግ ሊያግደን አይገባም:: አብረን ከመስራትም ሊያግደን አይገባም::

ዛሬ ነገ ሳንል  ተግባራዊ እንቅስቃሴ በማድረግ በሀገራችን ኢትዮጵያ የተጀመረውን የለውጥ ጉዞ  ማገዝ ኢትዮጵያዊ ኃላፊነታችንና ግዴታችን ነው:: ተግባር ከብዙ ቃል በላይ ይናገራል ይባላልና እራሳችንን በተግባር የምንፈትሽበት ጊዜ ነው:: ሀገራችን ከአምባገነናዊ ሥርዓት ተላቃ በሽግግር ላይ  ያለች እንደመሆኗ መጠን ከምንም ጊዜ በላይ የልጆቿ እገዛ  ያስፈልጋታል።

ለውጡን እንዴት ማገዝ እንችላለን?

ለውጡ ስር ነቀልና ዘላቂ እንዲሆን ከምንም በላይ የተቋማት ግንባታ ያስፈልጋል:: ሲቪክ ማህበራት፤ ነፃ የሚዲያ ተቋማት፤ ከፖለቲካ ፓርቲ ተፅእኖ የተላቀቀ ሲቪል ሰርቪስ እና ሌሎችም ለዲሞክራሲያዊ ሥርዓት አስፈላጊ የሆኑ ግብዓቶች በሙሉ እንዲሟሉ ዲያስፖራው በብዙ መልኩ እገዛ ማድረግ ይችላል። በርግጥ ዜጎች ከኤምባሲዎቻቸው ጋር መልካም ግንኙነት ቢኖራቸው ብዙ ለሃገር የሚበጅ ስራ መስራት ይቻላል። ጊዜው ሲደርስ ሁሉም ይሆናል። እስከዚያው ግን የሚከተሉትን ማከናወን ለሞራል እርካታ ከማገዙም በላይ ሀገራዊ ግዴታን ለመወጣት ይጠቅማል።

1.       የውይይት መድረኮችን፣ ኮንፈራንሶችን፣ ልዩ ልዩ ዐውደ ጥናቶችን በማዘጋጀት ህዝባችን የተገኙትን ለውጦች እውቀቱን፣ ገንዘቡን፣ ጊዜውን በመስጠት በተግባር ማገዝ እንዲችል ማበረታታት።
2.    ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመነጋገር ዜጎች የገንዝብ እገዛ እንዲያደርጉና ገንዘባቸውም ለታቀደለት ዓላማ እንዲውል ንቁ ተሳትፎ ማድረግ።
3.       ዜጎቻችን ወደ ሀገራቸው በመሄድ እወቀታቸውንና ጊዜያቸውን ለወገኖቻቸው እንዲያካፍሉ ማበረታታት።
4.       ዜጎቻችን ከሀገር ቤት የሚያገኙትን እውቀትና ልምድ በሚኖሩበት ሀገር ለሚገኙ ወገኖች ማካፈል የሚችሉበትን መድረክ ማመቻቸት።
5.       ዜጎች የውጭ ትምህርት እድል እንዲያገኙ ጥረት ማድረግ፣ አስፈላጊ ሆኖ ሲግኝ በተደራጀ መልኩ ማገዝ።
6.       ኢንቨስትመንት ወደ ሀገር ቤት እንዲገባ ማበረታታት::
7.       ሀገራችን ከቱሪስቶች ጉብኝት የውጭ ምንዛሬ ልታገኝ የምትችለበትን ሁኔታ መፍጠር
እነዚህንና ሌሎች ተግባራትን በተደራጅ መልኩ በማከናወን ሀገራዊ ግዴታን በመወጣት ከህሊና ወቀሳም መዳን ይቻላል። ከምንም በላይ ግን ለዲሞክራሲያዊ ተቋማት ግንባታ ዲያስፖራው ከፍተኛ እገዛ ማድረግ ይችላል ። ይጠበቅበታልም።

ቸር እንሰንብት።


አምባገነንነትን በጀብደኝነት ከተካን ወደ አምባገነንነት መመለሳችን አይቀርም

ጥቂት ' የፖለቲካ አክቲቪስቶች ' በኢትዮጵያ የተከሰተውን ለውጥ በግላቸው ያመጡት እንደሆነ ደጋግመው ሲያወሩ ይሰማል :: ግልፅ መሆን ያለበት የተገኘው ውጤት የመላው ኢትዮጵያውያን...