21 August 2018

ለበሬ ወለደ ዜና ቦታ የለንም


                             

የሶሻል ሚዲያ የውሸት ዜናዎች (Fake News) ሊያሸብሩን አይገባም!

በሀገራችን የተከሰተውን ለውጥ ተከትሎ ብዙ በሬ ወለደ ዜናዎች በሶሻል ሚዲያ ውጤቶች በተለይም በፌስ ቡክና ቲዩብ ( Facebook and You tube) በብዛት ተሰራጭተው እናያለን። እነዚህ የበሬ ወለደ ዜናዎች ብዙሃን ወገኖቻችንን ሊያሳስቱና ሊያስጨንቁ ይችላሉ። ህዝባችን የውሸት ዜናዎችን አጥብቆ መታገል ይገባዋል። ከምንም በፊት ለነዚህ የውሸት ዜናዎች ቦታ ባለመስጠት፤ አስፈላጊ ከሆነም የውሸት ዜናዎቹ በሚለቀቁበት ጊዜ የወሬዎቹን ምንጭ በመጠየቅ ብዙ ጥፋት ሳያስከትሉ ሊያስቆማቸው ይገባል።

የወሸት ዜናዎች በተለያዩ ምክንያቶች ሊፈጠሩ የሚችሉ ሲሆን የተለያየ አላማዎችም አሏቸው።

1. የፖለቲካ ለውጡን ለማወክ የሚደረግ ጥረት፥ በሀገራችን የተከሰተው ለውጥ ደጋፊ እንዳለው ሁሉ ተቃዋሚም አለው። ይህ ደግሞ በለውጥ ሂደት ውስጥ ብዙ ጊዜ የሚከሰት ነው። የፖለቲካና የኢኮኖሚ ጥቅማቸው የሚነካባቸው ግለሰቦችና ድርጅቶች በተቻላቸው መጠን የለውጥ ሂደቱን ከማወክ አይቆጠቡም። ለዚህም የተቻላቸውን ያህል በማድረግ ለወጡ እንዳይሳካና ህዝቡ በለውጡ ላይ ጥርጣሬ እንዲኖረው ለማድረግ ብዙ ጥረት ያደርጋሉ። ለውጡ እንዲቀለበስ ሌት ተቀን ተግተው ከመስራት አይቆጠቡም። እኩይ አላማቸውን ለማሳካት ብዙ ገንዘብ በማውጣት የተቻላቸውን ሁሉ ያደርጋሉ። ይህ የውንብድና ሥራ ብዙም ስለማያስኬድ በዚህ ተልካሻ ተግባር ላይ የሚሳተፉ ግለሰቦችና ድርጅቶች ሌሎች ለውጥ የማደናቀፍ ተግባራት ላይ ከመሳተፍ አይቆጠቡም። ህዝባችን በሀገራችን ለተከሰተው ለውጥ ዘብ በመሆን ለውጡን እንደ ዓይኑ ብሌን ሊጠብቀው ይገባል።

2. የገንዘብ ፍቅር፤ በገንዘብ ፍቅር የተለከፈ ሰው ለገንዘብ ሲል ብዙ አሳፋሪ ተግባራት ሊፈጽም ይችላል። በተለይ ከዩ ቲዩብ (You Tube) ለምትገኝ ጥቃቅን ጥቅማጥቅም ኃላፊነት የጎደላቸውና ምንጭ አልባ የውሸት ዜናዎች ሲለጥፉ እያየን ነው። በእንደዚህ አይነቱ ተልካሻ ተግባራት ላይ የሚሳተፉ ሰዎች ብዙውን ጊዜ የሚያሳስባቸው ምን ያህል ሰው የለጠፉትን ቪዲዮ እንዳየው ማወቅ በቻ ነው። ይህ ተግባር አሳፋሪ ነው። ሊታረምም ይገባል። ህዝባችንም አጥብቆ ሊታገለው ይገባል።

3. 15 ደቂቃ ታዋቂነት መሻት (15 minutes social media fame) የተለያዩ የውሸት ዜናዎችን በተለይ በፌስ ቡክ ላይ በመለጠፍ ለሚያገኙት ላይክ ( like ) ብቻ የሚጨነቁና ያም ታዋቂነት የሚያፈራላቸው የሚመስላቸወ ሰዎች አሉ። ይህ አይነቱ ተግባር በአብዛኛው በፌስ ቡክና ትዊተር ሲከሰት ይስተዋላል። ህዝባችን የዜናዎችን ምንጭ የመጠየቅ ባህል ሊያዳበር ይገባል። ሁሌም ሳናታክት ዜናው እንዴትና ከማን እንደመጣ መጠየቅ አለብን።

4. በየዋህነት የተነገረውን ሁሉ ማሰራጨት፤ ከዘመዴ፣ ከጓደኛዬ፣ ከውስጥ አዋቂ ምንጭ ያገኘሁት ነው በሚል የፈጠራና የውሸት ዜናዎች ሲሰራጩ ይታያል። አልፎ አልፎ የምናያቸው የውሸት ዜናዎች በየዋህነት የሚሰራጩ ናቸው። ጥንቃቄ ማድረግ ይገባል። በተለይ ከውስጥ አዋቂ ምንጭ እንዳገኘሁት የምትለዋ ሊሰመርባት ይገባል። ግልፅ መሆን ያለበት ሁላችንም የውስጥ አዋቂ ምንጭ ሊኖረን አይችልም። 100 ሚሊዮን ህዝበ ባለባት ሀገር ላይ 100 ሚሊዮን የውስጥ አዋቂ ምንጭ እንደመጥቀስ ነው። ጎበዝ ጦር ከፈታው ወሬ የፈታው ይሉ የለ አበው። ጠንቀቅ ማለት ይገባል። መጠየቅ፤ ተጨማሪ ምርምር ( research )ማድረግ ይገባል።
ለውጡን የመጠበቅ ኢትዮጵያዊ ግዴታ አለብን። በየጊዜው የሚፈጠሩ የውሸት ዜናዎች ሊያውኩንና ሊያሳስቱን አይገባም። አበከረንም ልንታገላቸውም ይገባል።

ለነ በሬ ወለደ ቦታ ባለመስጠት የለውጥ ጉዟችንን በጋራ እንጓዝ። ኢትዮጵያችንን በህብረትና በዓላማ ፅናት እንጠብቃት።

The Global Refugee Forum – time for meaningful participation of Refugees

  As the Global Refugee Forum takes place between 13 - 15 December 2023 in Switzerland, it is vital that we have meaningful participation of...