19 September 2018

አምባገነንነትን በጀብደኝነት ከተካን ወደ አምባገነንነት መመለሳችን አይቀርም


ጥቂት 'የፖለቲካ አክቲቪስቶች' በኢትዮጵያ የተከሰተውን ለውጥ በግላቸው ያመጡት እንደሆነ ደጋግመው ሲያወሩ ይሰማል:: ግልፅ መሆን ያለበት የተገኘው ውጤት የመላው ኢትዮጵያውያን የዘመናት የትግል ውጤት መሆኑን ነው:: ግለሰቦች ተነስተው ለውጡን እኔ ነኝ ያመጣሁት፤ እንደፈለገኝ መሆን እችላለሁ ሲሉ ዝም ብለን ልናያቸው አይገባም:: ዝምታ ባበዛን ቁጥር እነዚህ ግለሰቦች በጀብደኝነት ናላቸው ይዞራል:: በጀብደኝነት የሚሰራ ስራ ደግሞ ሚዛናዊነትን ሊያጣ ይችላል:: ችኩልነትም ይኖረዋል:: ለዚህም ነው ከአሁኑ ጥንቃቄ ማድረግ የሚገባን:: ሳይቃጠል በቅጠል ይባላል::

ከመንግሥት ከተፎካካሪ ፓርቲዎችና ከሚዲያው ምን ይጠበቃል?

1. ለሰላምና እርቅ በጋራ መሥራት - በሀገራችን ለዘመናት ሲዘራ የኖረው ዘርን መሰረት ያደረገ ቅስቀሳ በህዝቦች መካከል አለመተማመን መፍጠሩ አልቀረም:: ይህ አለመተማመን በለውጡ ላይ ተፅዕኖ አለው:: ተፅዕኖውም በግልፅ እየታየ ነው:: በህዝቦች መካከል ግልፅ የሆነ ውይይት ማድረግ አስፈላጊ ነው:: ችግሩ ምንድን ነው? የመፍትኄ ሃሳቡስ ብሎ መጠየቅና ጥልቅ የሆነ ውይይት ማድረግ ይገባል:: ችግሮችን አድበስብሰን ማለፍ የለብንም:: ችግሮቻችንን በውይይት የመፍታት ባህል ማዳበረ አለብን:: በሃሳብ አለመግባባት ወይም አለመስማማት ወደ ፀብ ሊወስደን አይገባም:: ላለመስማማት ተስማምተን አብረን መጓዝ እንችላለን (We need to agree to disagree):: ይህ ትልቅ የአመራር ብቃት ይጠይቃል::

2. ለተቋማት ግንባታ ቅድሚያ መስጠት - የተጀመረው ለውጥ መቀጠል የሚችለውና ዘላቂ የሚሆነው ለዲሞክራሲ ግንባታ አስፈላጊ የሆኑ ተቋማት በጊዜው ሲገነቡ ነው:: ከግለሰብም ሆነ ከፖለቲካ ፓርቲ ተፅዕኖ ነፃ የሆኑ ተቋማት ከገነባን ብቻ ነው በኢትዮጵያችን ዲሞክራሲያዊ ስርዓት ማስፈን የምንችለው:: እነዚህ ተቋማት ዋስትናዎቻችን ናቸው:: ስለዚህም ቅድሚያ ልንሰጣቸው ይገባል::

3. የሚዲያ ነፃነትና ተጠያቂነት - በሀገራችን ያሉት የሚዲያ ተቋማት ነፃነት ሊኖራቸው የሚገባውን ያህል ተጠያቂነት እንዳለባቸውም መዘንጋት የለባቸውም:: ጀብደኝነትንና የጥላቻ ወሬዎችን በተደጋጋሚ ማስተናገድ ዋጋ ያስከፍላል:: ለሀገርና የህዝብ ደህንነት ስጋት የሆኑ መልዕክቶች ከመተላለፋቸው በፊት ጥንቃቄ ማድረግ አስፈላጊ ነው:: የተጠያቂነት ባህልን ማዳበር ይገባል::

4. የሥራ ፈጠራና የኢኮኖሚ ግንባታ - በሀገራችን የሥራ አጥነት በስፋት መኖሩን መዘንጋት የለብንም:: ብዙ ሥራ መስራት የሚችሉ ነገር ግን የሥራ እድሉን ያላገኙ ወጣቶች እንዳሉ የታወቀ ሲሆን ይህንን እምቅ ኃይል ለሀገር ግንባታ ለመጠቀም ሁኔታዎችን ማመቻቸት አለብን:: ከሀገራችን ሀብቶች አንዱ የሰው ኃይላችን ነው:: የሥራ ፈጣሪነትን በማበረታታት ይህን እምቅ ኃይል ለሀገር ግንባታ ልናውለው ይገባል:: ይህ ኃይል የሀገራችን ኢኮኖሚያዊ ዋልታና ደጀን መሆን ይችላል:: ኢንቬስትመንት ወደ ሀገራችን እንዲገባና ህዝባችንም ተጠቃሚ እንዲሆን መንግስትም ሆነ የሚመለከታቸው አካላት በሙሉ ሳያሰልሱ መስራት አለባቸው:: በተጓዳኝም ሲቪል ሰርቪሱ ከተንዛዛ አሰራርና ሙሰኝነት ነፃ መሆን አለበት:: ለዚህም መሳካት ሁሉም የበኩሉን ማድረግ ይጠበቅበታል::

ሀገራችንን የማገዝና የማሳደግ ግዴታው የሁለችንም ነው:: ዛሬ ነገ ሳንል ሀገር ግንባታ ላይ ማተኮር አለብን::

As we mourn the departure of Neil Jameson, we cherish his legacy graciously

  Many people dream of doing good as in doing good is much satisfaction and fulfilment. Few are lucky enough to do good through out their li...