በሀገራችን ኢትዮጵያ የተከሰተውን
ለውጥ ተከትሎ ብዙሃን በስደት ዓለም ያሉ ወገኖች ወደ ሀገር ቤት የመመለስና ከወገን የመገናኘት እድል እንዳጋጠማቸው ሁሉ እኔም ከብዙ አመታት የስደት ቆይታ በኋላ ወደ ቅድስት ሀገር ኢትዮጵያ ከነመላ ቤተሰቤ ለመሄድ ችዬ ነበር:: በሀገር ቤት ያለውን ለውጥ በቅርበት የምከታተል ቢሆንም በተግባር ያየሁት ለውጥ ግን ከጠበኩት በላይ ነው:: አዎ እውነተኛ ለውጥ አለ:: እሰይ በርቱ ከማለት በተጨማሪ ለውጡ ዘላቂ እንዲሆን በተግባር ማገዝ የውዴታ ግዴታ ነው::
ታህሳስ 13 ቀን 2011 (ዲሴምበር 22 )
At the Office of the Mayor of Addis Ababa |
ይህ ቀን
አዲስ አበባ የደረስኩበት ቀን ሲሆን የመጀመሪያውን መልካም ስራ ያየሁት ቦሌ አለም አቀፍ ኤርፖርት ነው:: የመግቢያ ቪዛ ላይ የሚሰሩት የኢሚግሬሽን ሰራተኞች ቅንነት፣ ፍጥነትና ቅልጥፍና የመጀመሪያው የመልካም ስራ መገለጫ ሆኖ አግኝቸዋለሁ:: ከ30 ደቂቃ ባነሰ ጊዜ ውስጥ ትህትና የተሞላበት መስተንግዶ ማግኘት እጅግ የሚያስመሰግን ነው:: ይህ ቦታ ሀገራችን ሲደረስ የመጀመሪያው ቦታ ስለሆነ የሰራተኞቹ ብቃትና ቀናነት ብዙ ዋጋ አለው:: በርቱ ሊባሉ ይገባል::
አዲስ አበባ
የደረስኩት በምሽት ቢሆንም አዲስ ሞቅ ደመቅ እንዳለችና ከነ ግርግሯ ነበረች። ወደ ማረፊያዬ ጉዞ እያደረግኩኝ በነበረበት ሰዓት የነበረውን የመኪና ብዛትና የሚሯሯጡ ወጣቶች ስመለከት ብዙ ማሰቤ አልቀረም። ለምን ይሆን እነዚህ ወጣቶች በዚህ ምሽት የሚሯሯጡት ማለቴም አልቀረም። እነዚህ ወጣቶች አዲስ አበባ በውስጧ ብዙ የህይወት ገፅታዎች እንዳካተተች አመላካች ከመሆናቸው በተጨማሪ ብዙ መሰራት ያለባቸው ሥራዎች እንዳሉ ያሳየናል። የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ ታከለ ኡማ ይህንን አሳሳቢ ሁኔታ ከግምት ውስጥ በማሰገባት አፋጣኝ መፍትሄ ለመስጠት የነደፉት ፕሮጀክት ያለ መሆኑን በከንቲባው ቢሮ በተገኘሁብት ጊዜ የተረዳሁ ሲሆን ፕሮጀክቱ ውጤታማ እንዲሆንና በጎዳና ላይ ያሉትን ዜጎች መልሶ ለማቛቛም የሁሉም ሀገር ወዳድ ዜጋ ርብርቦሽን ይጠይቃል:: ተግባራዊ እገዛ ማድረግ ሀገሩና ወገኑን ከሚወድ ዜጋ የሚጠበቅ ነው።
With Selamawit Dawit, Director General of Ethiopian Diaspora Agency |
በአዲስ አበባ
ቆይታዬ ባየሁት የህዝብ ተስፋ ሙሉነትና የነፃነት መንፈስ በውስጤ ትልቅ ተስፋ እንድሰንቅ ያደረገኝ ሲሆን ለስራ በሄድኩባቸው እንደ ኢሚግሬሽን፣ ቴሌ፣ የውጭ ጉዳይ ሚ/ር፣ ዲያስፖራ ኤጀንሲና የአዲስ አበባ መስተዳድር ያየሁት የስራ ተነሳሽነትና የተጠያቂነት ስሜት በጣም ተደስቻለሁ::
በአዲስ አበባ
ብዙ መልካም ነገሮችን ለማየት የቻልኩትን ያህል ብዙ አሳሳቢ ነገሮች እንዳሉም ለማስተዋል ችያለሁ:: በከፍተኛ ደረጃ የሚጠቀሰው የስራ አጥነትና የትራንስፖርት ችግር ቢሆንም ብዙ ሊሰራባቸው የሚገባቸው ነገሮች እንዳሉ ግልፅ ነው:: የመብራት በየጊዜው መጥፋት፤ የውሃ በድንገት መሄድ መፍትሄ ሊበጅለት ይገባል:: የብር የመግዛት አቅም መውረድም አሳሳቢ ነው:: ብዙ አሳሳቢና ሊሰራበት የሚገባ ጉዳይ የመኖሩን ያህል
በህዝባችን ውስጥ ያለው ተስፋ በጣም አበረታች ነው:: ተስፋ ለስኬት አስፈላጊ የመሆኑን ያህል፤ ስኬት ደግሞ የተግባራዊ ስራ ውጤት ነው::
ዛሬ ነገ
ሳንል ሀገራችንን እንደየአቀማችን በተግባር እናግዝ:: ነጮቹ " Walk
the Talk” ይላሉ::