በሀገራችን የተከሰተውን ለውጥ ተከትሎ የፖለቲካ ምህዳሩ እየሰፋ የመጣ ቢሆንም በተጓዳኝም ዘረኝነትና ፅንፈኝነት መስፋፋቱ የአደባባይ ሚስጥር ነው። የመናገርና የመፃፍ መብት ለእሱ/ለእሷ ብቻ የተፈቀደ የሚመስላቸው ቡድኖችን እያስተዋልን ነው። የእኔ ሃሳብ ብቻ ነው ትክክለኛ ሃሳብ የሚሉ ግለሰቦችና ቡድኖች በብዛት እያየን ነው። የዲሞክራሲ ባህል ባልዳበረበት ሀገር እያንዳንዱ እንቅስቃሴያችን ጥንቃቄ ያስፈልገዋል። የፖለቲካ ልሂቅ (Political elite)ነኝ የሚሉ ሰዎች በየአጋጣሚው የሚሰጧቸው መግለጫዎችና አስተያየቶች አርቆ አስተዋይነትን ማዕክል ያደረገ መሆን አለበት። ከብሽሽቅ ፖለቲካና ከፀብ አጫሪነት መጠንቀቅ ይገባል። ጊዜው የዲሞክራሲያዊ ባህል ግንባታ እንጂ የነጥብ ማስቆጠሪያ አይደለም ።

ትልቁና አሳሳቢው ጉዳይ ፅንፈኝነት ነው። ጫፍና ጫፍ ሆኖ ማሸነፍ አይቻልም። መዘንጋት የሌለበት ጉዳይ አብዛኞው ህዝብ መሃል ላይ ያለ፤ ይበጀኛል የሚለውን ጠንቅቆ የሚያውቅና በጥሞና እየገመገመ ያለ መሆኑን ነው። ህዝብ የማያውቅ ከመሰለን ትልቅ ስህተት ውስጥ ነው ያለነው። ህዝብ በጣም ያውቃል።